
ባሕር ዳር፡ የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ለተደረገልኝ ደማቅ አቀባበል አመሠግናለሁ ብለዋል። በቆይታዬ በሰላም እና ጸጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ እና የተቀናጀ መሠረተ ልማት ግንባታን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ በተፈጥሮ ሃብት የታደለ፣ ለም መሬት፣ ንጹህ ውኃ እና የሰው ኃብት አለው ሲሉም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ራሳችንን ለመመገብ ትግል እያደረግን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) የጋራ ዓላማችንን ለማሳካት በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
“እንደ ቀጣና የጋራ ህልማችንን እውን ለማድረግ የሚያስችል እምቅ አቅም አለን” በተናጠል እንደማናድግ በመገንዘብ በትብብር ለመበልጸግ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል። ቀጣናዊ አስተሳሰብ እና በትብብር መሥራት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፤ ዕድገትና ብልጽግናን የማምጣት ህልማችንን እውን ለማድረግ ከሶማሊያ ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!