
አዲስ አበባ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ስለኢትዮጵያ መድረክ ሁለተኛ ምዕራፍ፣ ሁለተኛ መድረክ በሐረር ከተማ ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሐረር ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ስለኢትዮጵያ በተሰኘው መድረክ ስለሀገራችን አብሮነት የሚያወሱ አራት መነሻ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዝግጅቱም አብሮነትን የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚብሽን በይፋ ተከፍቶ ጉብኝት ተደርጓል። በውይይት መድረኩ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል። በመድረኩ የተገኙት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያ የበርካታ ባሕልና ኪነ ጥበብ ባለቤት ናት ብለዋል።
በተለይም ኪነ ጥበብ በሕዝቦች መካከል ድልድይ በመኾን አስተሳሳሪ ትርክት ለመፍጠር የሚያስችል መሳሪያ ነው። ይህንን ትልቅ ሀብት በመጠበቅ ሀገራዊ አብሮነታችንን ማጠናከር አለብን፣ ለዚህም የጋራ ሥራ ያስፈልገናል ብለዋል። ባሕልም ኾነ ኪነ ጥበብ የሕዝብ ስሜት መግለጫ መንገድ መኾኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ኪነ ጥበብ እና ባሕል በሕዝቦች መካከል ድንበርን በማስቀረት የጋራ መንገድን ለማኅበረሰቡ የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
በመኾኑ ሁላችንም ይህንን ማጠናከር እና ማስቀጠል ይገባናል ሲሉ አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ ከሀረር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!