በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን እየለማ ያለው መስኖ ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚኾን ነው።

36

ሁመራ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፣ በቃብትያ ሁመራ ወረዳ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የመስኖ ልማት ጉብኝት አድርገዋል። ጉብኝቱ የተደረገው የተከዜ ወንዝ ዳርቻን ተንተርሶ እየለማ በሚገኘው አካባቢ ነው። በጉብኝቱ የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳደሩ አሥተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት፣ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

አልሚ ባለሀብቶች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል። እንደ ጤፍ እና ሀብሀብ ያሉ በአካባቢው ያልተለመዱ ሰብልና ፍራፍሬን በድፍረት እያለሙ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። አካባቢውን የበለጠ ለማልማት እና ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀውን የነዳጅ ወጭ ለመቀነስ መንግሥት የሶላር አቅርቦት እንዲያመቻችም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳደሩ አሥተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት በጉብኝቱ ወቅት የተመለከቱት የመስኖ ልማት ለሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ጥሩ ተሞክሮ ሊኾን እንደሚችል ገልጸዋል። የመስኖ ልማቱ ከክልሉ አልፎ ለሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር ይችላል ብለዋል።

የሀብሀብ ልማት ለአካባቢው አዲስ መኾኑን የተናገሩት አማካሪው አልሚ ባለሀብቱ በድፍረት ማልማት መጀመሩ የሚደነቅ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል። የአልሚዎቹ ተግባር ከራሳቸው አልፈው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመኾኑ ሊበረታቱ እንደሚገባም ተናግረዋል። ምርቱ ወደ ገበያ ሲወጣ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል። በሸማቾች እና በአምራቾች መካከል ተጠቃሚነትን እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

አካባቢው ትልቅ የመስኖ ልማት አቅም እንዳለው የክልሉ መንግሥት ያውቃል ያሉት አማካሪው አካባቢውን ከዚህ በተሻለ ለማልማት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ደምጤ የተከዜን ወንዝ ተንተርሶ እየለማ ያለው መስኖ መንግሥት ያስቀመጠውን በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት አቅጣጫ እውን ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

ዝናብን ጠብቆ ብቻ ሳይኾን በአካባቢያችን ያለውን የውኃና የመሬት ፀጋ ተጠቅመን በዓመት ሦስት ጊዜ ማልማት እንደምንችል በተጨባጭ ያየንበት አካባቢ ነው ብለዋል። በዞኑ የለማው የመስኖ ጤፍ የሚያስደንቅ መኾኑንም ተናግረዋል። በስፍራው የሚለማው የመስኖ ሰብል በሌሎች አካባቢዎችም መልማት እንደሚችል ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- በአምሳሉ አሞኘ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

Previous article“ዘካ መስጠት፣ ሰደቃ ማድረግ እና በጎ ተግባራትን መፈጸም ይገባል” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሼሪአ ፍርድ ቤት
Next article“ኪነ ጥበብን የጋራ ትርክት ለመፍጠር ልንጠቀምበት ይገባል” ሸዊት ሻንካ