“ዘካ መስጠት፣ ሰደቃ ማድረግ እና በጎ ተግባራትን መፈጸም ይገባል” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሼሪአ ፍርድ ቤት

30

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የረመዳን ጾም ሲጾም የተቸገሩትን በመርዳት እና ለሀገር ሰላም በመጸለይ ሊያሳልፍ እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሼሪኣ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰይድ አሳስበዋል፡፡ ጾም ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች መካከል አንዱ ሲኾን በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እና በጎ ተግባራት የሚፈጸሙበት ነው፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ በዚህ የጾም ወቅት ራሱን ይበልጥ ወደ ፈጣሪ የሚያስጠጋበት እና መተሳሰብ እና አብሮነትን ይበልጥ የሚጎለብትበት ነው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሼሪኣ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰይድ የረመዳን ወር ሰዎች ስሜታቸውን የሚገቱበት ይልቁንም ተግተው በመጸለይ ከፈጣሪ ምንዳ የሚያገኙበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ለሶላት መትጋት፣ የተቸገሩትን መርዳት እና መተሳሰብን ማጎልበት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

“ዘካ መስጠት፣ ሰደቃ ማድረግ እና በጎ ተግባራትን መፈጸም ይገባል” ያሉት ሼህ ወለላው በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን እና የተቸገሩትን ወገኖች ማገዝ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ሼህ ወለላው ሰይድ በመልዕክታቸው ለሃይማኖት ተገዥ መኾን እና ሁሉም በየእምነቱ ለሀገር ሰላም መጸለይ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ግጭቶች መቋጫ እንዲያገኙ እና ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ የሰላም አማራጮችን ሁሉ መከተል አስፈላጊ መኾኑን ያሳሰቡት ሼህ ወለላው ሰይድ ለሰላም መስፈን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ4 ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ገለጸ።
Next articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን እየለማ ያለው መስኖ ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚኾን ነው።