
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ከ4 ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል። አርሶ አደር ወርቁ ቢምር በዋድላ ወረዳ 017 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እንደሚያመርቱ ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው የተሻለ የምርት ውጤት ማግኘታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መግዣ ወጭያቸውንም እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡ የዋድላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ መርቅ ብሩ በ2017 ዓ.ም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት 49 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።
ለአርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ስለ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሳይንሳዊ ዝግጅት ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ቦጋለ ሰጤ በ2017 በጀት ዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረት አቅደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት እና ጠቀሜታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ሳይንሳዊ ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ የኾነ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራው ከ300 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው ብለዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች ምርት ላይ ከፍተኛ የኾነ ለውጥ ማምጣቱን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!