
ጎንደር: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ከ1ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት የእንቦጭ አረም መወገዱን አስታውቋል። የጣና ኃይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
ውኃማ አካላትን መጠበቅ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት የተካሄደ ሲኾን እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል። የክልሉን የውኃ ሀብት ለመጠበቅ የተቋቋመው የጣና ኃይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጄንሲ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ሢሠሩ መቆየታቸውን የኤጄንሲው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዳዊት አቡ ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ1ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት የእንቦጭ አረም መወገዱን አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲዎችን እና የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር የጣናን ህልውና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን በሂደት ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ከውኃማ አካላት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን እንደሚሠራም ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የክልሉ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የውኃማ አካላትን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት እየተሠራ ቢገኝም ማኅበረሰቡን ከማሳተፍ አኳያ ቀሪ ተግባራት መኖራቸውን የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ ተናግረዋል። በተለይ በላይኛው የተፋሰሱ አካባቢዎች ላይ ተገቢው ሥራ ባለመሠራቱ ምክንያት ዉኃማ አካላት ለችግር መጋለጣቸውን ያነሱት ኀላፊው አሁን ላይ ግን የተሻሉ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ውኃማ አካላትን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሸጋገሩ የማድረግ ሥራ የቀጣይ ተግባር ይኾናልም ብለዋል። የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የልየታ ሥራዎችን በመሥራት ወደ ተግባር ለመግባት ጥረት ቢደረግም የሰላም እጦቱ በሚፈለገው ልክ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ ፈተና እንደኾነባቸውም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!