የአድዋ ድል ከታሪክ ሽሚያ እና ከተዛባ ትርክት ወጥቶ ሊዘክር ይገባል።

63

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአድዋ ድል የመሪ ጥበብ፣ የሕዝብ አንድነት እና ሕብረት የታየበት የነጻነት ድል መኾኑን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምሕርት ክፍል መምህር ሰጠኝ ጌታነህ (ዶ.ር) አስታውቀዋል። ትውልዱ ከታሪክ ሽሚያ እና ከተዛባ ትርክት ወጥቶ ሊዘክረው እና ሊማርበት እንደሚገባም መክረዋል።

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለመላ ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌት ነው። ነጮች በጥቁር ሕዝቦች ላይ የነበራቸውን የተዛባ ምልከታ እና አሉታዊ ተጽዕኖ የቀየረ፤ መለውን ጥቁር ሕዝብ ያስተሳሰረ ድል ነው ብለዋል መምህሩ። ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ተሰሚነት እንዲኖራቸው ያስቻለ ድል እንደኾነም ተናግረዋል።

የአድዋ ድል የመሪዎች የመሪነት ጥበብ፣ የሕዝቦች የሀገር ፍቅር እና አንድነት የታየበት እንደኾነ ነው የገለጹት። በአድዋ ድል ሀገራዊ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት፣ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የተገኘበት የአንድነት መሠረት ነው ብለዋል። ከትናንት አባቶች በመማር የውስጥ ችግሮችን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ልዕልና በጋራ መቆም የትውልዱ ኀላፊነት እንደኾነም ገልጸዋል።

ከተዛባ ትርክት እና ከታሪክ ሽሚያ በወጣ መንገድ አድዋዊ ትውልድ መገንባት ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ኀላፊነት ሊኾን ይገባልም ብለዋል የታሪክ መምህሩ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።
Next articleየሰላም እጦቱ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ ፈተና ኾኗል።