
ደሴ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን ከዞን የሥራ ኀላፊዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቺአምላክ ገብረማርያም ኮሚሽኑ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በሙሉ አቅም የአገልግሎት አሰጣጡ ውጤታማ እንዲኾን ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ወራት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት የታየባቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሠራኞችን የመረጃ አያያዝ ለማዘመን እና ከወረቀት ነጻ ለማድረግ ዲጂታላይዝድ እንዲኾኑ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። በቀጣይም የተገልጋዩን ማኅበረሰብ ጥያቄ በመገንዘብ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ይገባል ያሉት ኮሚሽነሯ የሚነሱ የአፈጻጸም ችግሮችን ማሥተካከል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የተሻለ የፈጸሙ ሠራተኞች ተገቢውን እውቅና እንዲያገኙ እና ክፍተት የታየባቸው ላይ ደግሞ እርምጃ በመውሰድ አገልግሎቱ እንዲሻሻል እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ ጭምር በማስደገፍ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዮችን ርካታ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!