
እንጅባራ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በቀጣይ ወራት የሚከናወኑ የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዎች የትውውቅ መድረክ በእንጅባራ ከተማ እያካሄደ ነው። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ሰውነት መድረኩ በቀጣይ 120 ቀናት የሚከወኑ ዋና ዋና የፓርቲ እና የመንግሥት ተግባራት ተገምግመው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ያስቀመጣቸውን መሠረታዊ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ወደ መሬት የምናወርድበት የተግባር ምዕራፍ መኾኑን ገልጸዋል። ባለፋት ጊዜያት መሠረታዊ የሚባሉ ምዕራፎችን አሳልፈናል ያሉት ኀላፊው ከመቀልበስ ምዕራፍ እስከ ማጽናት ምዕራፍ ድረስ ተጋድሎ አድርገናል ነው ያሉት።
ሰላምን እና ልማትን ለማጽናት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓልም ብለዋል። ሰላምን በማረጋጋት እና በማጽናት ምዕራፍ በርካታ ስኬቶች እና ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት ኀላፊው። የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በስኬት ተጠናቅቀው ሕዝቡ የልማት ቱሩፋት ተጠቃሚ እንዲኾን ማደረግ ይገባልም ነው ያሉት አቶ አለሙ ሰውነት።
በመድረኩ የተገኙት እና ድጋፍ ለማድረግ ከክልል የሄዱት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ያለፉት ጊዜያት የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት አፈጻጸም እንደሚገመገሙ ገልጸዋል። በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ በክልል ደረጃ እና እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር የታቀዱ ተግባራትን በማከናወን የሕዝቡን መደበኛ ኑሮ የሚሻሽልበት እና ከሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት መድረክ መኾኑን ገልጸዋል።
በጥምር የጸጥታ የሥራ ኀላፊዎች እና አባላት ከፍተኛ ተጋድሎ፣ በመሪዎች መስዋዕትነት እና በሕዝቡ ተሳትፎ ሰላምን ለማረጋገጥ በተሠራው ተግባር በክልሉም ኾነ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መጥቷል ነው ያሉት። “በተደረገው ከፍተኛ ትግል የሰላም መሻሻል መምጣቱንም” አንስተዋል። ሕዝቡ በተሠሩት ተከታታይ ሥራዎች አሁን ላይ የፀረ ሰላም አደጋን በመረዳት ከመንግሥት እና ከጸጥታ መሪዎች ጎን እየተሰለፉ ፀረ ሰላምን እያወገዙ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ልማት እና መልካም አሥተዳደር የሚመጣው እና የሚገኘው በሰላም ነው ብለዋል። ሕዝቡ የሰላም እጦት ሳይበግረው ሰላምን እየናፈቀ፣ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረገ፣ ልማት እያለማ መኾኑንም አንስተዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሁሉንም አካላት ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት።።
ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
