
አዲስ አበባ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በክልሉ የደረሰውን ጉዳት በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል የምክክር መድረክ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች፣ አምባሳደሮች እና አጋር አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ መድረኩ የክልሉን አኹናዊ ኹኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እና የሰብዓዊ ርዳታን ለሕዝባችን ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል። ክልሉ በጦርነት፣ በድርቅ፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን የገለጹት ርእሰ መሥተዳደሩ በአኹኑ ሰዓት በክልሉ ውስጥ የዘለቀው ግጭትም ትልቅ ፈተና ኾኖ መቀጠሉን አንስተዋል።
በሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉልህ አበርክቶ ያለውን የአማራ ሕዝብን ሰላም በማረጋገጥ ክልሉን መልሶ ለማልማት ከአጋር አካላት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች በክልሉ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ርእሰ መሥተዳደሩ ጠይቀዋል። የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) ክልሉ ባለፉት ዓመታት በደረሰበት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን አንስተዋል።
በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ እንደሚጠይቅ ያነሱት ቢሮ ኀላፊው የክልሉ መንግሥት በየዓመቱ ለመልሶ ግንባታ በጀት መድቦ ሲሠራ ቢቆይም ከጉዳቱ መጠን አንፃር መሸፈን አለመቻሉን ገልጸዋል። በመኾኑም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እና የሲቪል ማኅበራት ትርጉም ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
ክልሉ አኹን ያለበትን ወቅታዊ ኹኔታ በተመለከተ እና ሌሎችም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
