በዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ላይ የግድያ ወንጀል ፈጽሟል የተባለ ተጠርጣሪ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

151

ባሕር ዳር: የካቲት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ላይ የግድያ ወንጀል የፈጸመ ተጠርጣሪ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የጉበት፣ የቆሽት እና የሃሞት መስመር ሰብ ስፔሻሊቲ ሐኪም፣ ተመራማሪ፣ መምህር እና በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ባልታወቁ ኃይሎች መገደላቸው ይታወሳል።

ጥር 24/2017 ዓ.ም ምሽት 1፡30 ሰዓት ገደማ ዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ሥራ ቆይተው ጥበብ ግዮን ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እየሄዱ ባለበት ወቅት በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መገደላቸውን እና ፖሊስ ገዳዮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሠራ መኾኑን አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፖሊስ ባደረገው ክትትል አንደኛውን ተጠርጣሪ ገዳይ በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል ብለዋል። እሱባለው ነበረ የሚባል ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል ነው ያሉት።

ወንጀል ፈጻሚው ድርጊቱን መፈጸሙን ማመኑንም ተናግረዋል። ግድያው ጥቅም ፍለጋ መኾኑን ተናግረዋል። ፖሊስ የዶክተር አንዱዓለም ዳኘን ገዳዮች ለፍርድ እንደሚያቀርብ ቃል በገባው መሠረት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ነው የገለጹት። በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ተመሳሳይ ወንጀሎችን ይፈጽም እንደነበርም አንስተዋል።

በግድያ ወንጀሉ ከተሳተፉት ውስጥ የተያዘው ተጠርጣሪ ዋናው መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው እርሱን ያገዙ እና ግብረ አበሮቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፖሊስ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የፖሊስን ሙሉ መግለጫ እናቀርባለን።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መልካም መሪ ሕዝብን ወደ ብርሃን ያሸጋግራል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሶማሊያ ሞቃዲሾ ገቡ።