
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር በቀጣይ ወራት በሚከናወኑ የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዎች ዙሪያ የዕቅድ ኦረንቴሽን መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እና ሌሎች የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የሕዝቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና የመልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቀጣይ ከሕዝባችን ጋር በመኾን በርካታ ሥራዎችን መተግበር ይጠበቅብናል ብለዋል። መሪዎች በቀጣይ እስከ ታች እየወረዱ መደገፍ እና ውጤት ማምጣት የሕዝብን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ ኾኖ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ.ር) “መልካም መሪ ሕዝብን ወደ ብርሃን ያሸጋግራል” ብለዋል። መሪ ሕዝብን ማንቃት፣ ማስተባበር እና በዘላቂነት ከችግር ለማውጣት ቁልፍ ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት። እንደ ደብረ ታቦር ከተማ የሕዝቡን የመልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ከሥራ ኀላፊዎች ጋር የሚደረገው ውይይት መልካም እንደኾነ ገልጸዋል።
በአጭር ጊዜ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት። ሕዝብን በማንቃት እና በማሰለፍ ልማት እና ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም ተቀናጅቶ መሥራት እንዳለበት መግለጻቸውን ከደብረ ታቦር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
