የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።

76

ባሕር ዳር: የካቲት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ክልላዊ የኮሌራ ወረርሽኝ ምላሽ ምክክር አካሂዷል። ኮሌራ በዓይን በማይታይ ባክቴሪያ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በሽታው የሰውነትን ፈሳሽ እና ንጥረ ነገር በተቅማጥ እና በትውኪያ አማካኝነት እንዲወጣ በማድረግ ሰዎችን በአጭር ጊዜ ለሞት ይዳርጋል።

በሽታው በአማራ ክልል ከሐምሌ/2015 ዓ.ም ጀምሮ ተከስቶ በሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል። በ2017 ዓ.ም ደግሞ በሽታው ከታኅሳስ ጀምሮ በምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ ወረዳ ተከስቷል። የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ሥብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ አእላፍ አባ ኃይለ ማርያም ያሳይ እንዳሉት በበርሚል አካባቢ በሽታው ሐምሌ/2015 ዓ.ም ተከስቷል።

በዚህ ዓመትም በሽታው መከሰቱን ገልጸዋል። የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር፣ በቂ መጸዳጃ ቤት አለመኖር፣ የመጠለያ ችግር ለበሽታው ሥርጭት እንደምክንያት ተነስተዋል። በሽታውን ለመከላከል በጊዜያዊነት አገልግሎቱ እንዲቆም ተደርጓል፤ በአብያተ ክርስቲያናትም ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ችግሩን በቋሚነት ለመፍታት አጋር አካላት የንጹህ መጠጥ ውኃ እና በቂ መጸዳጃ ቤት ግንባታዎችን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ሐምሌ/2015 ዓ.ም በቋራ ወረዳ በርሚል በተከሰተው የኮሌራ በሽታ በወረዳው ብቻ ከ50 በላይ ሰዎች ሕይዎት አልፏል።

በሽታው በክልሉ በሚገኙ 58 ወረዳዎች ተሰራጭቶ የ90 ሰዎች ሕይዎት ማለፉንም አንስተዋል። በወቅቱ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ በሽታውን ለመቆጣጠር ተችሏል። ይሁን እንጅ ከታኅሳስ/2017 ዓ.ም ጀምሮ በቋራ ወረዳ በርሚል ዳግም በሽታው መከሰቱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ወረርሽኙን ለመከላከል ከተጠርጣሪዎች ናሙና ተወስዶ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል። ዋነኛ የበሽታው ምንጭ እና አባባሽ ምክንያቶችን የመለየት እና ለባለሙያዎች የኮሌራ ወረርሽኝ ቅኝት እና ምላሽ ሥልጠና ሥራ መሠራቱም ተገልጿል። በሁሉም ዞኖች የኮሌራ ወረርሽኝ ቅንጅታዊ ምላሽ ሥራ እንዲነሳሳ ተደርጓል። የተባበሩት መንግሥታት ወኪሎች እና ድርጅቶች በቦታው እንዲገቡ ተደርጎ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሠጥ ተደርጓል።

ማኅበረሰቡ መጸዳጃ ቤትን በአግባቡ መጠቀም፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ ምግብን ከመንካት፣ ከማዘጋጀት እና ከመመገብ በፊት እጅን በሳሙና መታጠብ፣ ውኃን አፍልቶ ወይም አክሞ መጠቀም፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ እና በትኩስነቱ መጠቀም እና የአካባቢ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የበሽታው ምልክት የታየበትን ሰው ፈጥኖ ወደ ሕክምና መውሰድ፣ ከታማሚው የሚወጣ ፈሳሽ ጋር ንክኪ ያላቸውን ዕቃዎች እና ቦታዎች በአግባቡ ማጽዳት ይገባልም ብለዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ እንዳሉት በክልሉ የኮሌራ ሥጋት ባለባቸው 44 ወረዳዎች የሚገኙ ባለሙያዎችን የማሠልጠን ሥራ ተሠርቷል። የሕክምና ቁሳቁሶችን የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

ማኅበረሰቡም መከላከል ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በቋራ በርሚል አካባቢ መጸዳጃ ቤቶች የመገንባት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ3 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር ተጀምሯል።
Next article“መልካም መሪ ሕዝብን ወደ ብርሃን ያሸጋግራል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)