
ጎንደር: የካቲት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2017 ዓ.ም የትምህርት ቤት የምገባ መርሐ ግብርን አስጀምሯል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የምገባ መርሐ ግብሩ ተማሪዎች ለትምህርት የሚኖራቸዉ የዓዕምሮ ዝግጁነት እና ትምህርታቸዉን ወደዉ እንዲማሩ ያለዉ ፋይዳ ትልቅ ነዉ ብለዋል።
ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ ትዉልድ እንዲኾኑም የምገባ መርሐ ግብሩን ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ባለፈዉ ዓመት ከሁለት ሺህ በላይ የሚኾኑ ተማሪዎች የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ እንደነበሩ ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ በዘንድሮው ዓመት የተጀመረዉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ህጻናት በአካል፣ በዓዕምሮ እና በሥነ ልቦና የዳበሩ እንዲኾኑ የምገባ መርሐ ግብሩን ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ ናቸው። በከተማ አሥተዳደሩ በ11 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎች የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
በምገባ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ የኾኑ ተማሪዎች መርሐ ግብሩ በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸዉን ነግረዉናል። የተማሪ ወላጅ ከኾኑት መካከል ወይዘሮ ካሳየ ጌታቸዉ እና አቶ ጸጋዉ አይቸዉ የምገባ መርሐ ግብሩ ለተማሪዎች የትምህርት አቀባበል እና የእርስ በርስ ግንኙት ያለዉ ፋይዳ ጉልህ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:-አዲስ አለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
