243 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተጥቷል።

62

ደብረ ብርሃን: የካቲት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከከተማ አሥተዳደር እና ከዞን መምሪያ ኀላፊዎች እና ቡድን መሪዎች ጋር በመተባበር የበጀት ዓመቱን የሰባት ወራት አፈጻጸም በደብረ ብርሃን ከተማ እየገመገመ ነው። በመድረኩ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ምቹ እድሎች ቢኖሩም ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ጥሬ ሀብት በርካሽ ሰጥተን የኢንዱስትሪ ምርቶችን በውድ ዋጋ ለመሸመት ተገደናል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። በባለፉት ሰባት ወራት ለ2 ሺህ 520 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ1 ሺህ 354 አዳዲስ ጥያቄዎች ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል። ጥያቄ ያቀረቡ ባለሀብቶችም 243 ቢሊዮን ብር ማስመዝገባቸውን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪ ሥራ ካሳ ከፍለዉ መሬት ለሚወስዱ ባለሀብቶች ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መለየት ተችሏል ነው የተባለው፡፡ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ደግሞ 41 ሺህ 373 ሄክታር ገደማ መሬት መለየቱን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በአምራች ዘርፉ ለ155 ባለሀብቶች እና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩት 131 ባለሀብቶች መሬት ማስተላለፍ ተችሏል፡፡

ባለፉት ሰባት ወራት 111 አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደ ማምረት ገብተዋል ብለዋል ። በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ደግሞ 153 ፕሮጀክቶች ወደ ምርት ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በክልሉ ሥራ የጀመሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች 64 ሺህ 76 ቶን ምርት ወደ ውጪ በመላክ 61 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

በአበባ ልማት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ 1 ሺህ 143 ቶን ምርት ልከው 6 ነጥብ 18 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል፡፡ ተኪ ምርቶችን ከማምረት አንጻር 258 ሺህ 909 ቶን በማምረት 332 ነጥብ ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል፡፡ ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻር በአጠቃላይ በሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፍ በ7 ወራት 36 ሺህ 985 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡

የአሠራር ማዕቀፎችን ከማሻሻል ጀምሮ አምራች ኢንዱስትሪዎች እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 27 ባንኮች ተሳተፉ።
Next article“ትልቁ ሃብት ሰብዓዊ ሃብት ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ