
ደብረ ብርሃን: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ኃይል እና ባትሪ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ተካሂዷል::የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ.ር) ዓለም በከፍተኛ የአየር ብክለት እየተፈተነች ነው ብለዋል::
የምንጠቀማቸው የኃይል አማራጮች ለአየር ብክለት አጋላጭ ከመኾናቸውም ባሻገር አላቂ የተፈጥሮ ሃብቶች በመኾናቸው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ታዳሽ ኃይሎች ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በችግር ፈች ጥናት እና ምርምሮች ላይ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የተሠሩ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተሳሰር ወደ ትግበራ ማስገባት እንደሚገባም አሳስበዋል:: በሲምፖዚየሙ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ ይዘንጋው ይታይህ ለዓለም የሙቀት መጠን መጨመር አጋላጭ ከኾኑ ምክንያቶች አንዱ የትራንስፖርት ዘርፉ መኾኑን ገልጸዋል::
በትራንስፖርት ዘርፉ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለኃይል አማራጮች የሚወጣውን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ለመቀነስ የታዳሽ ኃይልን መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል:: ለዚህም የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ታዳሽ ኃይል ለመቀየር የሽግግር ሥራዎች በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሲምፖዚየሙ ታዳሽ ኃይል እና የባትሪ ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና የመንግሥት ተቋማት የተገኙ ምሁራን እና ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል።
ዘጋቢ:- ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
