
ደሴ: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በበጋ መስኖ የለማ የስንዴ ሰብልን ጎብኝተዋል። በደቡብ ወሎ ዞን ከ2 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬትን በበጋ መስኖ ስንዴ በመሸፈን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው።
በዞኑ ታርሶ የማያውቅ መሬት በማረስ ስንዴ ለማልማት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ገልጸዋል። ለማሳያነትም በቃሉ ወረዳ የሚገኙ ታርሰው የማያውቁ ሰፋፊ መሬቶችን ወደ ምርት ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል። ከነዚህ መሬቶች የሚገኘው ምርት በድርቅ እና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚጠቁ ወገኖች ድጋፍ እንደሚውልም አቶ አሊ ተናግረዋል።
የዞኑን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ በማምረት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። በቃሉ ወረዳ የለማው የበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኝ ቢኾንም በዞን ደረጃ የታቀደው ምርት እንዲገኝ ሰብሉን በቂ ውኃ በማጠጣት የበለጠ እድገቱ እንዲጨምር መሥራት እንደሚጠይቅ በመስክ ምልከታ አረጋግጠናል ብለዋል።
በቃሉ ወረዳ ከ1 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ በመሸፈን ከ56 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መኾኑን የወረዳው አሥተዳዳሪ ሙሕዲን አሕመድ ተናግረዋል። አሁን ላይ የውኃ እጥረት ያጋጠመ ቢኾንም በጀኔሬተር በመግፋት ሰብሉን በቂ ውኃ በማጠጣት ምርማነቱን ለመጨመር እንደሚሠሩም አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴን በማልማት የክልሉን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ለውጭ ገበያ የሚውል ምርት ለማምረት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አምሳሉ ጎባው ተናግረዋል። በ2017 ዓ.ም በክልሉ ከ254 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን ከ190 ሺህ ሄክታር መሬትን በዘር መሸፈን መቻሉንም አቶ አምሳሉ አስረድተዋል።
በጸጥታ ችግር ውስጥ ቢኾን የተሠራው የመስኖ ስንዴ ልማት አበረታች ስለመኾኑም ገልጸዋል። በሄክታር እስከ 40 ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተዘራው የስንዴ ሰብል ቁመና የታቀደውን ምርት ለመሠብሠብ የሚያስችል ምቹ ኹኔታ መኖሩን አመላካች ነው ብለዋል።
ከበጋ መስኖ ልማት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ከበጋ መስኖ ስንዴ ለማግኘት የታቀደውን ምርት ለማግኘት የተባይ አሰሳን ጨምሮ የአረም እና ሌሎች የሰብል እንክብካቤ ሥራዎች ከወዲኹ በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ መኾናቸውንም አቶ አምሳሉ ገልጸዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነት የሉዓላዊነት መገለጫ ጭምር እየኾነ መምጣቱን ያነሱት አቶ አምሳሉ የክልሉን የመልማት አቅም ተጠቅሞ ስንዴን በብዛት እና በጥራት ማምረት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
