
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ማተቤ መረቁ የእንጅባራ ዙሪያ ነዋሪ ሲኾኑ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ወንዝ በመጥለፍ በመስኖ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን እያለሙ ይገኛሉ። አርሶ አደሩ በ2015/16 የመስኖ ምርት ዘመን ያለሙትን ሽንኩርት፣ ድንች እና ቲማቲም በመሸጥ በተለምዶ ፋራ ሞተር የሚባል ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ በመግዛት ለግብርና ሥራቸው አጋዥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በ2016/17 ከመስኖ ያገኙትን ምርት በመሸጥ ሁለት ልጆቻቸውን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር መጀመራቸውንም ገልጸዋል። ሌላዋ አርሶ አደር እህትነሽ የኔው የዶንዶር ወንዝን ጠልፈው በበጋ መስኖ እያለሙ እንደኾነ ገልጸውልናል። ዘንድሮ በበጋ መስኖ እያለሙት ያለው የስንዴ፣ የድንች፣ የሽንኩርት እና የቃሪያ ልማት በጥሩ ቁመና ላይ በመኾኑ ጥሩ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀዋል። አርሶ አደሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ መስኖ የማልማት ልምዳቸው እየተሻሻለ መምጣቱንም ትዝብታቸውን አጋርተዋል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ከ39 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። ከ20 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ስንዴ እየለማ መኾኑን የጠቀሱት አቶ አዲሱ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ነው ብለዋል። ምርጥ ዘርም በጊዜው በአርሶ አደሮች ፍላጎት መሠረት መሠራጨቱን ገልጸዋል።

“ከመስኖ ልማት 1ሚሊዮን 500 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል” ነው ያሉት አቶ አዲሱ። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው 342 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ47 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል ብለዋል። በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ192 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን ነው አቶ አጀበ የተናገሩት። ለዚህም ከ263 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እና ከ305 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል።
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሰብል ተመራማሪው ወለላው ሰንደቅ (ዶ.ር) መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከነደፋቸው ስትራቴጂዎች መካከል የመስኖ ልማትን ማስፋፋቱ በመልካም የሚታይ ነው ብለዋል። አነስተኛ የይዞታ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች ወንዞችን በመጥለፍ፣ የከርሰ ምድር ውኃን ቆፍረው በማውጣት እና የዝናብ ውኃን በማቆር በመስኖ ማልማት በምግብ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለገበያ እንዲያቀርቡ እያስቻላቸው መኾኑን ምሁሩ አንስተዋል።
አርሶ አደሮች መስኖ ልማት ላይ የፈለጉትን ዓይነት ዘር በፈለጉት መሬት ላይ መዝራት ብቻ እንደሌለባቸው ይመክራሉ። ሥነ ምኀዳሩን ታሳቢ ያደረገ፣ ኩታ ገጠምን የዋጀ፣ የባለሙያን ምክረ ሐሳብ የተከተለ፣ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መኾን ግድ ይላል ነው ያሉት። በዘመናዊ መስኖ የሰብል ዓይነቶችን መርጦ እና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ተጠቅሞ ማልማት አስፈላጊ ነው ያሉት ተመራማሪው ይህን ማድረግ ከተቻለ ከስንዴ በሄክታር 45 ኩንታል ምርት ማግኘት ይቻላል ይላሉ።
ይህ የሚኾነው ግን ዘመናዊውን አሠራር መከተል ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
