ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ጋር ጥምረቱን አጠናክሮ እንደሚሠራ የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።

32

ወልድያ: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳደር በዞኑ ከሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር የስድስት ወራት አፈጻጸምን የሚገመግም የጋራ መድረክ አካሂዷል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በልማት ዘርፍ እና በአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ዘርፍ የተሠማሩ መኾናቸው ተገልጿል።

የሰሜን ወሎ ዞን ገንዘብ መምሪያ ኀላፊ ጀነቲ አያሌው በዞኑ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የያዙ 48 ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዞኑ፣ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እየሠሩ ነው ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 24ቱ በልማት ሥራ የተሰማሩ ሲኾኑ 18 ድርጅቶች በአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ተሰማርተው ኅብረተሰቡን እያገለገሉ ነው ብለዋል።

ድርጅቶቹ በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ስምምነት ወስደው እየሠሩ መኾናቸውን የገለጹት ኀላፊዋ ከሦሥት ወር እስከ አምስት ዓመት ቆይታ እንዳላቸው ነው ያስረዱት። ቆይታቸውን አጠናቀው ሲወጡ ውል የተፈራረመው መንግሥታዊ ተቋም ተረክቦ በዘላቂነት ለመሥራት የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን ኀላፊዋ ገልጸዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ታምራት ንጋቱ ዞኑ ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ጋር ጥምረቱን አጠናክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ድርጅቶቹ በውኃ ልማት፣ በምግብ አቅርቦት እና ድጋፍ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በሰላም እሴቶች ግንባታ እንዲኹም በሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

በድግግሞሽ ለ3 ሚሊዮን 188 ሺህ 453 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡን የሰላም እና የልማት ባለቤት ማድረግ ይገባል” ጎሹ እንዳላማው
Next articleየአርሶ አደሮችን ህይወት እያሻሻለ ያለው የበጋ መስኖ።