“ሕዝቡን የሰላም እና የልማት ባለቤት ማድረግ ይገባል” ጎሹ እንዳላማው

33

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የመንግሥት እና የፖለቲካ የቀሪ ወራት እቅድ ሥራዎችን ገምግሟል። የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለባሕር ዳር እምርታዊ እድገት ይበጃሉ ተብለው የተያዙ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅዶች ታቅደው እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።

በቀሪ ወራት የእቅድ ሥራዎችን ባለፉት ስድስት ወራት ያልተከናወኑ ተግባራትን በመጨመር የከተማዋን ሁለንተናዊ ለውጥ ሊያረጋግጥ የሚችል ተግባር መፈጸም ተገቢ ነው ብለዋል። የባሕር ዳር ከተማ ልማት እና ሰላም ግንባታ እውን የሚኾነው በመሪው እና የጸጥታ መዋቅሩ ብቻ ሳይኾን በመላ ማኅበረሰቡ የላቀ ርብርብ እና ያልተቋረጠ ድጋፍ ጭምር የሚረጋገጥ በመኾኑ ሕዝቡን የሰላም እና የልማት ግንባታ ባለቤት ማድረግ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከባሕር ዳር ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በየጊዜው የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እና አጠቃላይ የሕዝቡን ኑሮ አሻሽሎ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሰላም ከማስፈን ጎን ለጎን ስኬታማ የገቢ አሠባሠብ ተግባር መፈጸም፣ ሕገ-ወጥነትን መከላከል፣ የመልካም አሥተዳደር ግንባታ ተግባራትን በትኩረት ማከናወን ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መኾኑን አሣሥበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጊዜው ታከለ ሕዝቡ የባለቤትነት ስሜትን ተላብሶ ለጋራ ጉዳይ በአንድነት ተቀናጅቶ እንዲሠራ በማድረግ ከተማዋ ከስጋት ነፃ ኾና ሰላም እና ፍትሕ እንዲሰፍንባት ከፍተኛ ጥረት የማድረግ ተግባር ዋነኛው ጉዳይ እንደኾነ አንስተዋል።

በመሬት ዘርፍ እና መልሶ ማልማት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲኹም ጥራት እና ተደራሽነት፣ በሕገ-ወጥ ድርጊቶች መከላከል፣ በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት፣ በሥራ እድል ፈጠራ ከ20 ሽህ በላይ ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎች በቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዘርፎች ማሳተፍ ተችሏል ብለዋል።

የንግድ እና ገበያ ልማት ዘርፉን በማጠናከር የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት በመፍጠር የኑሮ ውድነትን በመቀነስ፣ በገቢ አሠባሠብ፣ በግብርና፣ በአሳ እና እንስሳት፣ በሴፍትኔት ዘርፎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በትምህርት፣ በጤና እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተያዙ እቅዶችን አብራርተዋል። መረጃው የባሕር ዳር ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደብረ ብርሃን ከተማ ያለው የኢቨስትመንት እንቅስቃሴ ለሌሎች ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው” አቶ መላኩ አለበል
Next articleከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ጋር ጥምረቱን አጠናክሮ እንደሚሠራ የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።