
ደብረ ብርሃን: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በደብረ ብርሃን ከተማ አምስት ፋብሪካዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል። በደብረ ብርሃን ከተማ በፍጥነት እያደገ የመጣው የኢንቨስትመንት ልማት የማኅበረሰቡ ሰላም ውዳድነት ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ “በከተማዋ ያለው የኢቨስትመንት እንቅስቃሴ ለሌሎች ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው” ብለዋል፡፡
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መካሄዱ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በክልሉ ወደ ምርት እንዲገቡ ያስቻለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የክልሉ ኢዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የኢንቨስትመንት ልማቱነሰ ሳይበግረው በበጀት ዓመቱ 111 በአዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ለኢንቨስትመት ልማት ምቹ በመኾኑ በርካታ ፕሮጀክቶችም ይመጣሉ ብለዋል።
በቀጣይም አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ ማነቆዎችን መፍታት፣ ምርታማነትን መጨመር እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚንነት የማረጋገጥ ተልዕኮ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማዋ ከ660 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 120 ያህሉ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ሂደት ገብተዋል ብለዋል።
በከተማዋ 120 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ለልማት ጉዞው መሳካትም የከተማው ሰላም ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት። በከተማው የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ወደ ተግባር ያልገቡ ስምንት ፕሮጀክቶች የወሰዱት መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ነው አቶ በድሉ የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
