“የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአካባቢ ብክለትን በማስቀረት በኩል የሠራቸው ተግባራት ምሳሌ የሚኾኑ ናቸው” ማኅተመ ኃይሌ (ዶ.ር)

44

ደሴ: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የደሴ ከተማ ሕዝብ ተወካይ የኾኑት ማኅተመ ኃይሌ (ዶ.ር) የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል። “ሆስፒታሉ የአካባቢ ብክለትን በማስቀረት በኩል የሠራቸው ተግባራት ለሌሎች የሕክምና ተቋማትም ምሳሌ እንደሚኾን” ተናግረዋል።

ማኅተመ ኃይሌ (ዶ.ር) ይህን ያሉት የሆስፒታሉን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች እና አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከቱበት ወቅት ነው። በጉብኘታቸውም ታካሚዎችን አግኝተው አነጋግረዋል። የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ መኾኑን ማረጋገጣቸውንም አንስተዋል። ሆስፒታሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጀመር የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።

በቅርቡ ሥራ የጀመረውን የሥነ ደዌ/ፓቶሎጂ/ ምርመራ ክፍልን በምሳሌነትም አንስተዋል። የሥነ ደዌ ምርመራ እና ህክምና ክፍሉ ግብዓት እንዲሟላለት የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል። የአልትራሳውንድ ምርመራ ክፍሉ የተሻለ አገልግሎት ሲሰጥ መመልከታቸውንም ገልጸዋል። በምልከታቸው የሆስፒታሉ የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ዘመናዊ እና አካባቢን ከብክለት የሚታደግ መኮኑን ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል።

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ “ቀልጣፋ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ የማይሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በቅርቡ ለመጀመር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ ስለመኾኑም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወቅቱ በቅንጅት ወደ ሥራ በመግባት ሕዝባችን የናፈቀውን ሰላም የምንመልስበት ነው” አቶ ጥላሁን ደጀኔ
Next article“በደብረ ብርሃን ከተማ ያለው የኢቨስትመንት እንቅስቃሴ ለሌሎች ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው” አቶ መላኩ አለበል