
ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን እና የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የሕግ ማስከበር ሥራዎች አፈፃፀምን እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን እየገመገመ ነው። የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “ወቅቱ ፅንፈኝነት ሀገር አፍራሽ መኾኑን በመረዳት በቅንጅት እና በቁርጠኝነት ሠርተን ሕዝባችን የናፈቀውን ሰላም የምንመልስበት ነው” ብለዋል።
የሕግ ማስከበር ሥራው በርካታ ድሎችን የተቀዳጀንበት፣ ሕዝባችንን ከአፍራሽ አጀንዳ የለየንበት፣ በርካታ የጽንፈኛው ቡድን አባላት የሰላም ጥሪውን የተቀበሉበት፣ ረጅም እርቀቶችን በመጓዝ ሃሰትን ከእውነት የለየንበት ወቅት ነው ብለዋል። የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የፅንፈኛው ቡድን አባላት ተደጋጋሚ የተሃድሶ ሥልጠና ውሰደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓልም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ክልሉ በአንፃራዊ ሰላም ውስጥ ይገኛል ብለዋል። የክልሉ ሕዝብ በፅንፈኛው ቡድን እገታ፣ አፈና፣ ዝርፊያ፣ ግድያ እና ግጭት ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶበታል” ነው ያሉት።
የቆዩበት የተሳሳተ የትግል ስልት ቁጭት ውስጥ ያስገባቸው የፅንፈኛው ቡድን አባላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ነው። ሰልጣኞቹ መንግሥት እና ሕዝብ የጀመረውን የሰላም ማስከበር እና የልማት አጀንዳዎች እውን ለማድረግ እና የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ ቃል ገብተው በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። በመድረኩ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
