
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሐረሪ ክልል ለአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ከሚሴ አጠቃላይ ሆስፒታል ግምታቸው ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችና መሣሪያዎችን ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ ለኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ አስረክበዋል።
ሚኒስትሯ በርክክቡ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ እርስ በርስ መደጋገፍ በጤናው ዘርፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አንዱ መንገድ በመሆኑ የሐረሪ ክልል መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ ድጋፉ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱን ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ትሥሥር የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል። የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ድጋፉ የጤና አገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፤ ለሐረሪ ክልል ሕዝብና መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ድጋፉ ካሁን በፊት የከሚሴ ሆስፒታል የህክምና ግብአት እጥረት መነሻ በማድረግ ለዞኑ ሕዝብ አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ በተገባው ቃል መሠረት የተደረገ መሆኑ መገለጹን የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
