
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልዕክት የዕውቅና እና የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መልዕክት አስተላልፈዋል። ርዕሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት ግብርን በአግባቡ ማሥተዳደር በክልሉ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነጻ ለመውጣት፣ የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ እና የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር ገቢን ማሳደግ የማይተካ ሚና እንዳለው ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። የገንዘብ፣ የቁስ እና የሰብዓዊ ሃብቶችን መፍጠር እና ማከማቸት ወሳኝ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ “የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር በአግባቡ መሠብሰብ ይገባል” ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የታክስ አሥተዳደሩን ማዘመን እና በቴክኖሎጅ የመደገፍ ሥራ ቢሠራም አሁንም ለታክስ አሥተዳደሩ ተገዥ ያለመኾን ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። ግብር ከፋዩም ግብር መክፈል ኩራት መኾኑን በመረዳት የተጣለበትን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጣ አሳስበዋል። በየደረጃው የሚገኙ የተቋማት የሥራ ኀላፊዎችም የገቢ አሠባሰብ ሥርዓቱ እንዲሻሻል በሚደረገው ጥረት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
በመልካም ሥነ ምግባር ላገለገሉ ባለሙያዎች እና በቅንነት እና በታማኝነት ግብር ለከፈሉ ግብር ከፋዮችም ምስጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
