
አዲስ አበባ: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፓርቲው በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ውሳኔዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማት ማኅበረሰቦች ማብራሪያ ሰጥቷል። ፓርቲው ከ15 ሚሊዮን በላይ አባላት ማፍራቱን የገለጹት በብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ነብዩ ስሁል ያስመዘገባቸውን ስኬቶች እና የነበሩ ተግዳሮቶችን ለዲፕሎማቶቹ አብራርተዋል።
በተለይም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ሀገሪቱን የወደብ ባለቤት እንድትኾን ለማስቻል የተሠሩ ተግባራትን ጨምሮ በርካታ ለውጦችን ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል። “ለዓለም ተምሳሌት የሚኾን ብልጽግናን ለማምጣት እንደሚሠራም” ተናግረዋል። የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በክፍተት ያነሱት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ሰላምን ማጽናት፣ የጋራ ትርክትን መገንባት፣ የሕዝቡን የኑሮ ጫና መቀነስ፣ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እና አጠቃላይ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት በማፋጠን ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን መገንባት ፓርቲው በቀጣይ የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት ውስጥ በዋናነት የሚሠራባቸው ዘርፎች ናቸውም ብለዋል። ከዲፕሎማቶች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውም በፓርቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ ቢቂላ ሁሬሳ (ዶ.ር) ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በፓርቲው ውሳኔ እና አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ተመሳሳይ መድረክ በቀጣይም በውጭ ሀገራት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ዘጋቢ: ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!