“ለሀገር እና ክልል አቀፍ ፈተና ተማሪዎችን እያዘጋጀሁ ነው” የምሥራቅ ጎጃም ትምህርት መምሪያ

18

ደብረ ማርቆስ፡ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ አንጻራዊ ሠላም በተፈጠረባቸው ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ እና ለክልል አቀፍ ፈተና ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ገልጿል። መምሪያው በ110 የመጀመሪያ እና በ32 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሟላ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

ሀገርን በዘላቂነት ለመገንባት ትምህርት ወሳኝ ነው። በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ትምህርት በበርካታ አካባቢዎች ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል ብለዋል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን አኹን በተፈጠረው የሰላም እና መረጋጋት ኹኔታ የሦስተኛ ዙር የተማሪ ምዝገባ በመፈጸም የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን የመምሪያው ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ልጆቻችን መማር አለባቸው የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው። ልጆች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ሁሉም አካል ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል። አሁንም ገና ወደ ሥራ ያልገቡ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል። ቀደም ብለው በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ሥራቸውን በጀመሩ ትምህርት ቤቶች ላይ ተማሪዎችን ለሀገር አቀፍ እና ለክልል አቀፍ ፈተና ብቁ እንዲኾኑ እና ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾኑ አቶ ጌታሁን አስገንዝበዋል።

የትምህርት ዘርፍ የብዙ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ እና ሰላምን የሚሻ በመኾኑ ለውጤታማነቱ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይጠይቃልም ብለዋል። በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መጠገን እና መገንባትም ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ስለመኾኑ አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ክልሉ የበለጠ እንዲያድግ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ሀብት ማመንጨት አለባቸው” ዓይናለም ንጉሴ
Next articleእየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ለማጽናት የኅብረተሰቡ አጋርነት ሊጠናከር ይገባል።