
ባሕር ዳር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ”ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልዕክት የእውቅና እና የታክስ ንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው። በመድረኩ የተገኙት የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ የግብር ንቅናቄ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት እንደኾነው ገልጸዋል።
ግብር መሠብሠብ የየትኛውም ዓለም መንግሥት የሚከውነው የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት፣ ሰላም ለማስፈን፣ የሀገርን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማሻሻል እንደኾነም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የታክስ አሥተዳደር ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢታዩበትም የሚሠበሠበው ገቢ ግን በቂ አለመኾኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ የመልማት አቅም ያላት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለተለያዩ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች የተመቸች ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ በአማራ ክልልም ትልቅ የመልማት አቅም እንዳለ አንስተዋል።
ክልሉ የበለጠ እንዲያድግም የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ሀብት ማመንጨት አለባቸው ብለዋል። ዛሬ እውቅና የምንሰጣቸው እና የምንሸልማቸው ግብር ከፋዮች በክልሉ ታላላቅ ኢንቨስትመንት ጀምረው የሥራ ዕድል የፈጠሩ እና ለኤክስፖርት የሚያመርቱ ናቸው ነው ያሉት። አማራ ክልል የወደፊት የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል የታክስ አሠባሠብ ውስንነት ያለበት እንደኾነ ገልጸዋል።
በ2016 ዓ.ም አፈጻጸማችን 512 ቢሊዮን ብር ተሠብሥቦ የዓመቱ አፈጻጸም ተጠናቋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ። የዘንድሮው የሰባት ወር አፈጻጸም ካለፈው ዓመት አፈጻጸም አንጻር 519 ቢሊዮን ብር ተሠብስቦ የተሻለ ቢኾንም እንኳ ከሀገራችን የመልማት ፍላጎት አኳያ ሲታይ ግን ገና የሚቀረው መኾኑን ገልጸዋል።
በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍም ካሉት ቅርንጫፎች የተሻለ ገቢ የሚሠበስብ መኾኑን ጠቅሰው በሀገር ደረጃ የተሠበሠበው 101 በመቶ ቢኾንም የአማራ ክልል ግን እስካሁን የሠበሠበው የእቅዱን 80 በመቶ ነው ብለዋል። ግብርን ለመሠብሠብ ግብር አመንጭ አካላት ጥሩ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እና ጥሩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
ይህ ባለመኾኑ እና ግብር በአግባቡ ባለመሠብሠቡ የዜጎችን የመልማት ዕድል እና እንደ ሀገር የብልጽግናን ሀገር የማሳደግ ራዕይ እንደሚያደናቅፍ አመላክተዋል። አማራ ክልል ሁሉም ሀብቶች ያሉት ኾኖ ሳለ ወደ ኋላ የሚያስቀሩትን ነገሮች በመተባበር መቅረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሁሉንም አቅሞች ለልማት ብቻ እንዲውሉ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ሚንስትሯ አሳስበዋል።
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የክልሉ መሪ እና ሕዝቡ በጋራ ኾኖ ለሰላም ባደረጉት ጥረት አንጻራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉን አመስግነዋል። የንቅናቄ መድረኩ ታማኝ ግብር ከፋዮች የሚበረታቱበት እና ለቀጣይ ተልዕኮ የሚወሰድበት ነውም ብለዋል። በታክስ አሥተዳደር ሥርዓቱ ያሉ ችግሮችን በጋራ የምንታገልበት፤ የደረሰኝ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ድክመትን ለማሻሻል እና የኮንትሮባንድ ችግሮችንም ለመፍታት በትኩረት የምንሠራበት እንዲኾን አደራ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!