ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ገቢ ተሠብስቧል።

45

ባሕር ዳር፡ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልዕክት የእውቅና እና የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው። በመድረኩ የክልል ገቢዎች ቢሮ ኅላፊ ክብረት ማሕሙድ እንዳሉት የክልሉ ገቢ በአራት እጥፍ አድጓል።

መንግሥት ዘርፈ ብዙ የኾኑ የኀብረተሰብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ቁልፉ መሳሪያ የገቢ አቅምን ማሳደግ መኾኑን ተናግረዋል። መንግሥት ሀገርን ማስቀጠል እና ሕዝብን መምራት የሚችለው የጸጥታ እና የገቢ አቅም ሲኖረው ነው ያሉት አቶ ክብረት መንግሥት ያለ ግብር ኀልውና የለውም ብለዋል።

ሀገራዊ ሪፎርም ከተካሄደ ወዲህ የክልሉ የገቢ አሠባሠብ በአራት እጥፍ ማደጉን አውስተዋል። በበጀት ዓመቱ የሰባት ወራት አፈጻጸም የተሠበሠበው ገቢ ወደ 31 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል።

የክልሉ ጸጥታ ባይደፈርስ ኑሮ የተሻለ የግብር አሠባሠብ ይኖር እንደነበር ቢሮ ኀላፊው አብራርተዋል። የክልሉ የምርት ዕድገት ለሀገር ከሚያበረክተው አንጻር እና ከክልሉ ኢኮኖሚያ አኳያ በክልሉ የሚሠበሠበው ገቢ ክልሉን እንደማይመጥን አቶ ክብረት ተናግረዋል። በመኾኑም ይህን መሰሉ የግብር አሠባሠብ ንቅናቄ ለማስፈጠሪያነት ያገለግላል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ አምስት ፍብሪካዎች ሥራ ጀመሩ።
Next article“ክልሉ የበለጠ እንዲያድግ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ሀብት ማመንጨት አለባቸው” ዓይናለም ንጉሴ