“የልጆቼን መልክ ዛሬ አየሁ” ታካሚ እናት

33

ወልዲያ: የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሂማሊያን ካታራክ ኘሮጀክት ጋር በመተባበር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና በነጻ እየሰጠ ይገኛል። ወይዘሮ ጦይባ ሙሀመድ የሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ለዓመታት ብርሃናቸውን በማጣታቸው ከቤት መዋላቸውን ነግረውናል።

“የጠፋብኝን የልጆቼን መልክ ዛሬ አይቻለሁ” ያሉት ወይዘሮ ጦይባ ወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባገኙት የነጻ ህክምና ብርሃናቸው ተመልሷል። የልጆቻቸውን መልክ ድጋሚ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። የወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ፍስሃ የኋላው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና በዘመቻ እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል።

የአሁኑ ዘመቻ እስከ የካቲት 21/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነው። ጥቅምት 2018 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ሁለት ሺህ 500 ወገኖቸን ለማከም አቅዶ እየሠራ መኾኑን ለአሚኮ ገልጸዋል። በዘመቻው የሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ እና የአጎራባች ዞን ወገኖችን ይስተናገዳሉ ብለዋል።

ባለፉት ወራት የቅድመ ልየታ ሥራ ተከናውኗል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ይህን መረጃ ሲሰሙ የሚመጡ ታካሚዎችንም ለማስተናገድ ሆስፒታሉ ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል።

የዓይን ሞራ ግርዶሽ በደም ግፊት፣ በስኳር በሽታ፣ በከባድ ምት እና በሌሎች ምክንያቶች የዓይን ብርሃንን የማጣት ክስተት ነው ያሉት የወልዲያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ህክምና ክፍል አሥተባባሪ ሙሉ ዳርጌ በቀላል ቀዶ ጥገና ህክምና ሊድን ይችላል ነው ያሉት። ተስፋ ቆርጠው ከቤታቸው የተቀመጡ ወገኖች ወደ ህክምና እንዲሄዱም መክረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የእውቅና እና የታክስ ንቅናቄ እያካሄደ ነው።
Next articleበደብረ ብርሃን ከተማ አምስት ፍብሪካዎች ሥራ ጀመሩ።