
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከዚህ በፊት መቼ የፀሐይ ግርዶሽ ተከስቶ ነበር? ቀጣይስ ይህ ታሪካዊ ክስተት መቼ ይከሰታል? ለሚሉ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
በመጪው ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ እንደሚከሰት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ ከምዕራብ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚታየው እና የቀለበት ቅርጽ እንደሚኖረው የተገለጸው የፀሐይ ግርዶሽ ከጠዋቱ 12፡45 እስከ ቀኑ 6፡33 ይቆያል፡፡ ከረፋዱ 3፡40 ደግሞ ለ38 ሴኮንዶች ጨለማ ይሆናል፡፡ በተለይም በከፊል ጎጃም፣ ጎንደር እና ወሎ የሚከሰት ሲሆን ከሌሎች አካባቢዎች ጨለማ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሰሎሞን በላይ (ዶክተር) ለአብመድ እንዳሉት ከሌሎች ቦታዎች በተለዬ መልኩ ደግሞ ላልይበላ ላይ ድቅድቅ ያለ ጨለማ ይሆናል፡፡
ኮንጎ ተነስቶ፣ ሱዳን፣ የመን፣ አማን፣ ፓበኪስታን፣ ህንድ እንደሚከሰት፣ ቻይና እና ኢትዮጵያ ተከስቶ ፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ እንሚያበቃም ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ ለየት ያለ ክስተት እንደሚኖር ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች እና ተሪስቶች ቀደም ብለው ያውቁ ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዕቅድ ይዘው ነበር፡፡ ኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ መልካም ገጽታዋን የምታስተዋውቅበት አጋጣሚ ስለሆነ ለዚህ ተግባር ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች እና ጎብኝዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ባይመጡም ኢንስቲትዩቱ ከፌዴራል እና ከአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ከኮማንድ ፖስት ጋር በመነጋገር በላልይበላ ሊከበር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
የላልይበላው ከሌሎች አካባቢ ለምን ተለዬ ስንል ላነሳነው ጥያቄ ዶክተር ሰሎሞን በሰጡት ምላሽ በፀሐይ እና በመሬት አቀማመጥ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው ጨረቃ በፀሐይ እና በመሬት መካከል ስትሆን እና ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ ብርሃን መስጠት ሳትችል (ጨለማ ስትሆን) በሚፈጠር ክስተት ነው፡፡ ይህም ላቅ ያለ ሥነ ፈለካዊ ክስተት እና ሀገር በቀል ዕውቀትን ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያገናኝ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በ1545 ዓ.ም፣ ሕዳር 5/1661 ዓ.ም፣ መጋቢት 24/1672 ዓ.ም እንዲሁም በ1720 ዓ.ም ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ዶክተር ሰሎሞን “ቀለበታዊ ግርዶሽ በኢትዮጵያ ድጋሚ የሚከሰተው ከ18 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚኖረው ደግሞ ከ146 ዓመታት በኋላ ነው” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ ከረጅም ዓመታት በኋላ የሚከሰተውን ታሪካዊ ክስተት ሕዝብ ሳይደናገጥ በዕድለኛነት ስሜት በነጻነት፣ በንቃት እና በጥንቃቄ ሊከታተለው እንደሚገባም መክረዋል፡፡
እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ማኅበረሰቡ ክስተቱ ሊያመልጣቸው አይገባም፡፡ (ኢንስቲቲዩቱ የሚያከፋፍለው እንዳለ ሆኖ ብዙኃን መገናኛዎችም የግርዶሽ መመለክቻ በመያዝ፣ ቴለስኮፕና ካሜራ ሲስተም በመጠቀም ከተቻለ በሄሊኮፕተር እና በድሮውን ካሜራ ይህንን ታሪክ ክስተት በጥንቀቄ በመቅረጽ ለተውልድ ማስቀረት ይኖርባቸዋል፡፡
በሚከሰትመበት ጊዜ በባዶ ዓይን ማየት እንደማይገባም መክረዋል፤ ክስተቱ በተፈጥሮ ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይኖረው እና ምናልባት የአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ ሁነቱ የዓለም የሕዋ ዘርፍ ተመራማሪዎች ሰፊ ምርምር እንዲያደርጉ እና የሕዋ ዘርፉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ እና ለቀጣይ ከፍተኛ ዝግጅት ለማድረግ በር ይከፍታል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ