የባለድርሻ አካላትን በአጀንዳ ማሠባሠብ ምክክር ምዕራፍ ማሳተፍ።

20

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 በተሰጠው ሥልጣን እና ኅላፊነት መሰረት የምክክር አጀንዳዎችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሕዝባዊ ውይይቶች እና ሌሎች አግባብነት ባላቸው መንገዶች እየሠበሠበ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ቁልፍ የምክክር ምዕራፍ ሲተገብር በክልል፣ በፌደራል እና በዲያስፖራው ማኅበረሰብ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ከግምት በማስገባት እንደኾነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞው በክልል የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሠባሠብ ምክክር ምዕራፍን ተግብሯል። የፌደራል ባለድርሻ አካላትም በሂደቱ የሚሳተፉበትን መድረክ በቅርቡ ለማዘጋጀት እየተሰናዳ ይገኛል፡፡ ለመኾኑ በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በዚህ ሂደት ማሳተፍ ለምን አስፈለገ? ከዚህ ቀጥሎ ያሉ ሐሳቦች ይህንን ጥያቄ ያብራራሉ፡፡

1.ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ

-በአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት የሚሳተፉ የፌደራል ባለድርሻ አካላት እንደሀገር ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገባቸውን የፖሊሲ ጉዳዮች ነቅሰው በመለየት በአጀንዳነት የማንሳት ዕድል አላቸው፡፡ እነዚህ አካላት በመዋቅራዊ ቁመናቸው በፖለሲ ደረጃ ሊገለጹ የሚችሉ ጉዳዮችን የሚሠሩ በመኾናቸው በዚህ ሂደት መሳተፋቸው ጠቃሚ እንደኾነ ይታመናል፡፡

2.በሁለት እና ከዚያ በላይ ክልሎች መካከል ያሉ ጉዳዮችን ለማስተናገድ

የፌደራል ባለድርሻ አካላት በተሰጣቸው አሥተዳደራዊ መዋቅር መሰረት በተለያዩ ክልሎች መካከል የሚነሱ የጋራ ጉዳዮችን ያስተናግዳሉ፡፡ ሂደቱ በሁለት እና ከዚያ በላይ በኾኑ ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ የድንበር፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ በፌደራል ባለድርሻ አካላት በአጀንዳነት ሊቀርቡ የሚችሉበትን ኹኔታ ለማመቻቸት ይረዳል፡፡

3.አካታችነትን ለማስፈን
በፌደራል የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ላይ በንቃት መሳተፋቸው ኮሚሽኑ በሁሉም ደረጃ የሚገኘውን የአሥተዳደር መዋቅር ማካተቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ሂደቱ በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው የጋራ በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይቶችን እንዲያደርጉ መንገዱን ከማመቻቸቱም በላይ የምክክሩ ውጤትም ተግባራዊ እንዲኾን በጎ ሚና እንዲጫወቱ ያግዛል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ዓመታትን የተሻገረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሠራለን” አቶ አደም ፋራህ
Next articleየአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የእውቅና እና የታክስ ንቅናቄ እያካሄደ ነው።