“የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ዓመታትን የተሻገረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሠራለን” አቶ አደም ፋራህ

29

ባሕር ዳር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በቱርክዬ አክ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተካፍለዋል።

አቶ አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የቱርክዬ አክ ፓርቲ ባካሄደው የፓርቲው 8ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመገኘት በብልጽግና ፓርቲ እና በአክ ፓርቲ መካከል በጋራ ለመሥራት የተፈራረምነው የመግባቢያ ሰነድ ተግባራዊነት እንዲጸና አንድ እርምጃ ወደፊት መጓዝ ችለናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ 129 ዓመታትን በተሻገረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመንግሥት ለመንግሥት፣ በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ የተፈጠሩ ግንኙነቶች የተገኙ ውጤቶችን በብልጽግና እና በአክ ፓርቲ ስምምነት የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን በማጠናከር በቀጣይ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እመርታዎችን ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ችለናል ነው ያሉት።

በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ እና በቀጣናዊ፣ በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያለው ትብብር እና እየተገኙ ያሉ ለውጦች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በብልጽግና ፓርቲ እና በአክ ፓርቲ መካከል ጠንካራ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት መፈጠሩ ተጨማሪ እድሎችን የሚከፍት ነው ብለዋል።

አክ ፓርቲ ባካሄደው 8ኛው ጉባዔ ላይ ረጂፕ ጣይብ ኤርዶጋን የፓርቲው ሊቀመንበር ኾነው በመመረጣቸው እና ሎሎች በጉባዔው ለፓርቲ መሪነት ለተመረጡ በሙሉ በብልጽግና ፓርቲ ስም እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ነገ ያካሂዳል።
Next articleየባለድርሻ አካላትን በአጀንዳ ማሠባሠብ ምክክር ምዕራፍ ማሳተፍ።