ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ነገ ያካሂዳል።

32

ባሕር ዳር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 60 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው። ጨረታው ለሁሉም ባንኮች ክፍት እንደሚኾን ተመላክቷል፡፡ ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በተለይም የወጪ ንግድ፣ ሐዋላ እና የካፒታል ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን አንስቷል፡፡

በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበረታች መኾኑንም ገልጿል፡፡ የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር ሪፎርሙ ጥሩ እና አውንታዊ ውጤት ቢኾንም የማዕከላዊ ባንኩን ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲ እና የዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ ነው ያስገነዘበው፡፡

በመኾኑም ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማገናዘብ እና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑን ከኤፍቢሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ኹኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ሽያጮችን እንደሚያካሂድ ተጠቅሷል፡፡ ይህም የባንኩን የዋጋ እና የውጭ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን ያስቀመጠው ስትራቴጂያዊ ግብ አካል መኾኑን ነው የገለጸው፡፡
ባንኮች በተቀመጠው መስፈርት እና የጊዜ ማዕቀፍ መሠረት በጨረታው እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በብዝኃነት አያያዝ ልምድ የሚወሰድባት ሀገር መኾኗን የሞሮኮ ልዑካን ገለጹ።
Next article“የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ዓመታትን የተሻገረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሠራለን” አቶ አደም ፋራህ