የሰላም ጥሪን መቀበል እና ሰላምን አማራጭ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

34

ጎንደር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከዞን እና ከወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በጸጥታ፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል። መድረኩ በዞኑ የሚገኙ አካባቢዎችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ ያለመ ነውም ተብሏል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ መሪዎች እና የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር ለጸጥታ መዋቅሩ ሥልጠና መስጠቱን ያነሱት አሥተዳዳሪው በዞኑ ያለውን የጸጥታ መዋቅር ለማደራጀት ተሠርቷል ብለዋል።

ለተሠሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል እና የፖለቲካ መሪዎች ቅንጅት ጉልህ ሚና እንደነበረውም አስታውቀዋል። ሁሉም ሁኔታዎች በጦርነት አይቋጩም ያሉት አሥተዳዳሪው በቀጣይም የሰላም ጥሪን ማቅረብ እና ሰላምን አማራጭ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ከዚህም ባሻገር ለማኅበረሰቡ ትክክለኛ መረጃዎች ተደራሽ እንዲኾኑ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ሕዝብን በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አስታውቀዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አንተነህ ታደሰ የዞኑ አሁናዊ የጸጥታ ሁኔታው የተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። የታጠቁ ኀይሎች በውይይት የመንግሥትን ሰላማዊ ጥሪ እንዲቀበሉ መሠራቱን ገልጸዋል።

በዚህም ከ824 በላይ የታጠቁ ኀይሎች የሰላምን ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠናን መውሰዳቸውን ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ማኅበረሰቡ ሰላምን በእጅጉ የሚሻ መኾኑን አንስተዋል። በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ የልማት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ሰላም ቀዳሚ ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል ።

ዘጋቢ፦ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትልቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት የኅብረተሰብ ተሳትፎ ሚናው ጉልህ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል መሥተዳድር ምክርቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።