
ባሕር ዳር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በቢሮ ኀላፊ ደረጃ የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ አማካሪ ሺቤ ክንዴ በሰጡት መግለጫ ቢሮው በከተማ ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉት በተለይም በከተማ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች አጠቃላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቢሮው የሥራቸው ባህሪ የሚያገናኛቸው ዘጠኝ ዋና ዋና ተቋማትን በማስተባበር እየተመራ መኾኑን ገልጸዋል። በተቀናጀ መልኩ በመሠራቱም ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል። በመሠረተ ልማት ዘርፍ የኮሪደር ልማት በሰባት ከተሞች እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ጎንደር፣ ኮምቦልቻ እና ባሕር ዳር የመጀመሪያውን ዙር አጠናቅቀው ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ እየገቡ መኾኑም በመግለጫው ተመላክቷል።
የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ እና የሥራ ባሕልን እየቀየረ ነውም ብለዋል። ልማቱ ኅብረተሰቡም በምቾት እንዲንቀሳቀስ ማስቻሉን ጠቅሰዋል። በክልሉ ሰባቱ ከተሞች 48 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት መንገድ ለመሥራት ታቅዶ 32 ኪሎ ሜትሩ በሥራ ላይ መኾኑን አቶ ሺቤ ገልጸዋል። 27 ሄክታር የአረንጓዴ እና ፓርክ ልማት እና 3 ነጥብ 7 ሄክታር የሕዝብ አደባባይ፣ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ መብራት እና ማስዋብ ሥራም የልማቱ አካል መኾኑን ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ጣና ሐይቅን ከከተማው ጋር በማገናኘት የልማቱ አካል መደረጉን የገለጹት አቶ ሺቤ የኅብረተሰቡን ይሁንታ ያገኘ እና ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ ለ37 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩም በመግለጫው ተወስቷል። በልማቱ 1ቢሊዮን ብር በኅብረተሰቡ ድጋፍ እንደሚደረግ ታቅዶ እስካሁን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መሳካቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ልማቱን በማስተዋወቅ ለበለጠ ተሳትፎ የማነሣሣት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል። በመደበኛ የመሠረተ ልማት ሥራም በክልሉ 500 ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑ ተገልጿል። ያደሩ ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ መኾኑን እና የበጀት ዓመቱን ፕሮጀክቶችም እስከ ሰኔ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን አቶ ሺቤ ተናግረዋል።
344 ሚሊዮን 262 ሺህ ብር በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በጉልበት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ መኖሩንም ጠቅሰዋል። ከተሞችን የአረንጓዴ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግም ትኩረት መሰጠቱን እና ባለፈው የተከላ ጊዜ 25 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!