ዓድዋ የአንድነታችን ማሰሪያ ውል ነው።

30

ባሕር ዳር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሥነልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደ ኪዳን እንደገለጹት 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ መልዕክት በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ይከበራል። በዓሉን ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው።

ለበዓሉ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ ተደራጅቶ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል። በበዓሉ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት። በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ እና የዓድዋ መታሰቢያ ሀውልት ሥር አበባ ይቀመጣልም ብለዋል። በዓሉ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የሚከበር ሲኾን፣ በዓድዋ መታሰቢያ የተለያዩ መርሐግብር ይካሄዳል፤ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም መልዕክት ያስተላልፉበታል ነው ያሉት።

በዓሉ በውጭ ሀገራት በሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች እንዲኹም በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በፖሊስ እንደሚከበር ነው የተገለጸው። በበዓሉ ላይ ዓድዋን እንዘክራለን ኢትዮጵያን አጽንተን እናሻግራለን፤ ዓድዋ የአንድነታችን ማሰሪያ ውል ነው፤ ዓድዋ የሉአላዊነታችን እና የነጻነታችን ምልክት ነው፤ ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ነው የሚሉ መልዕክቶች እንደሚተላለፉም ጠቁመዋል። የዓድዋ ድል በዓል የካቲት 23 ነው በድምቀት የሚከበረው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሆሳዕና ከተማ ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።
Next articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የሚሳተፉበትን መድረክ ሊያዘጋጅ ነው።