ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው አረጋውያን ከኮሮና የበለጠ መጠንቀቅ እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

159

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም (አብመድ) የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው አረጋውያን በልዩ ሁኔታ ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ አጋላጭ ሁኔታዎች እንዲጠብቁ እየተመከረ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑና በተለያዮ የሕክምና ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች የቆዩ የጤና ችግሮች ካሉባቸው ተጓዳኝ በሽታዎችን የመቋቋም ኃይልን ስለሚያሳጧ ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች በላይ መጠበቅ እንዳለባቸው የሕክምና ባለሙያዎች እየመከሩ ነው፡፡ ለእነዚህ ተጓዳኝ ሕመሞች የሚታዘዙ ስቴሮይድ ይዘት ያላቸው መድኃኒቶች በባሕሪያቸው ሌሎች በሽታዎችን የመቋቋም አቅምን የሚፈታተኑም ናቸው፡፡

እንደ ስኳር፣ የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት፣ ጉበት፣ ካንሰር፣ አስም እና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች የኮሮና ቫይረስ በሽታ ቢይዛቸው የከፋ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ በጥብቅ ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ የድንገተኛና ጽኑ ሕክምና ስቴሻሊስቱና የኮሮና ቫይረስ ሕክምና አማካሪው ዶክተር ወልደሰንበት ዋጋነው አሳስበዋል፡፡

‘‘ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከዚህ በፊት በነበረባቸው ሕመም ምክንያት የተዳከመው በሽታን የመቋቋም አቅም በኮሮና ቫይረስ ድንገት ቢያዙ እንኳ ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል፤ ለዚህ መፍትሔውም ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ ነው’’ ብለዋል ዶክተር ወልደሰንበት፡፡

በተለይ ደግሞ የካንስር ታማሚዎች ሌሎች ተጨማሪ ሕመሞች ካጋጠሟቸው የበሽታ መቋቋም ኃይላቸው ድሮም ቢሆን የተዳከመ በመሆኑ አስከፊ ሁኔታን ይዞ ስለሚመጣ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ዶክተር ወልደሰንበት አሳስበዋል፡፡

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፍንጫን በጭምብል ወይም እንደ አንገት ፎጣ ባሉ አዘውትሮ መሸፈን፣ አዘውትሮ እጆችን በንጹሕ ውኃና ሳሙና መታጠብ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ዓይነተኛ መንገዶች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ

Previous articleበትግራይ ክልል አራት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።
Next articleየሜካናይዜሽን ግብርና ተግባራዊ በማድረጋቸው ምርታቸው በእጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡