በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ የሥራ ጉብኝት አደረገ።

30

ባሕርዳር: የካቲት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ልዑኩ ጉብኝቱን ያደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሃሙድ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ፤ በቀጣይ በሞቃዲሾ የቴክኒክ ውይይት እንዲደረግ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡

በጉብኝቱ ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኀይሎች የመከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጀነራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ እና የሀገሪቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አምባሳደር አብዱላሂ መኀመድ አሊ ለልዑኩ ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት አዛዡ እና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል እየጠነከረ የመጣውን ግንኙነት አድንቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ለቀጣናዊ ሰላም እያበረከተች ያለችውን አስተዋጽኦም አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው የሰከነ ዲፕሎማሲ እና ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለአህጉሪቱ ሰላም የላቀ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኀይል (አሚሶም) ተልዕኮ ላይ ያለውን የላቀ ሚናም አንስተዋል።

እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ ለሶማሊያ መረጋጋት መስዋዕትነት ለከፈሉ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኀይል (አሚሶም) ፣ አትሚስ እና ሌሎች የጸጥታ ኀይሎችም ዕውቅና እና ክብር ሰጥተዋል።

በአሚሶም እና አትሚስ የተመዘገቡ ድሎችን አጽንቶ ማስቀጠል ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ያለውን ፋይዳም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የጦር ኃይሎች እና የመረጃና ደኅንነት ተቋማት መሪዎች በሶማሊያ እና በቀጣናው ስላለው የጸጥታ ሁኔታ በመምከር ፤ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋት ያላት ሚና በአድናቆት ተነስቷል። የአንካራው ስምምነት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መኾኑም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ተቋርጠው የነበሩ መሠረተ ልማቶች ወደ ሥራ እየገቡ ነው።
Next articleለሀገር የተከፈለ ዋጋ