
ፍኖተሰላም: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በማኅበራዊ፣ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ እድሜአለም አንተነህ ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር የበጀት ዓመቱን የልማት እና የአሥተዳደር ጉዳዮች በፍኖተ ሰላም ከተማ ገምግሟል።
ባለት ስድስት ወራት ተቋርጠው የነበሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ወደ ሥራ መግባት መቻላቸውንም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።
የልማት እና የአሥተዳደር ጉዳዮችን ምላሽ ለመስጠት ባለሙያዎች እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ማኅበረሰቡን እንዲደግፉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ 285 ሺህ 289 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን 12 ሚሊዮን 400 ሺህ ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አስማረ ተናግረዋል።
ኀላፊው የመሬት እና የውኃ ሀብትን ለማልማት በ155 ቀበሌዎች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን ደግሞ 1 ሚሊዮን 76 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን የገለጹት ኀላፊው 161 ሺህ ኩንታል ወደ ዩኒኖች ማስገባት ተችሏል ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ከመቆጣጠር አንጻር 22 ሺህ 337 ሊትር ነዳጅ፣ እና ሌሎችንም ምርቶች መያዝ መቻሉን በዞኑ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ ሀብታሙ ሞላ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት 54 ሚሊዮን 393 ሺህ ብር በጀት በመመደብ ለመንግሥት ሠራተኛው እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ለ74 ሺህ 888 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት 10 ሺህ 157 ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ሥራ እና ስልጠና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አያልሰው ሙሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ተሰራጭቶ የነበረውን ተዘዋዋሪ ብድር በማስመለስ ሌሎች ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!