“አንድ ከኾንን የማናሸንፈው ነገር የለም” ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ

27

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ከታላቅ ሕዝብ የሚጠበቅ ታላቅ ሀሳብ አግኝተናል ነው ያሉት። ሀሳባችሁን ሰጥታችሁ፣ ሀሳብ ወስዳችሁ የጋራ ሀገር ለመገንባት ቁርጠኛ በመኾናችሁ ኮርቸባችኋለሁ ነው ያሉት።

አንድ ከኾን የማናሸንፈው ነገር የለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በአንድነት ታላቅ ታሪኮችን እየጻፍን መጥተናል ብለዋል። አሁንም በአንድነት ኾነን የማናሸንፈው ፈተና የለም ነው ያሉት።

ለጠንካራ ሀገር ጠንካራ ፓርቲ፣ ጠንካራ መንግሥት እና የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ መሪ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ሁላችንም ሚናችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ጠላቶቻችን ደካማ ክልል እና ሀገር እንዲኖረን ማድረግ ነው ሀሳባቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ከሴራ ፖለቲካ እና ከአጥፍቶ ጠፊ አካሄድ በመውጣት ለሕዝብ ጥቅም መሥራት ይገባል” ነው ያሉት።

ለሕዝብ የሚጠቅመው አንድነት እና አንደኛው የሌላኛውን ሕመም መስማት ነው ብለዋል። የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ አጀንዳ ተደርገው እየተሠራባቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎች በፍጥነት እንዲመለሱ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅም አንስተዋል። በሰላም እጦት ያጣነው ነገር ሊያስቆጨን ይገባል ነው ያሉት።

የሕዝብን የኑሮ ውድነት የሚያቃልሉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በቁጭት እና በእልህ ለተሻለ ውጤት መሥራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። ፓርቲው ቃል የገባውን የሚፈጽም እና ለኢትዮጵያ አንድነት የሚሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ናይል የተስፋና የአንድነት ምልክት ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ተቋርጠው የነበሩ መሠረተ ልማቶች ወደ ሥራ እየገቡ ነው።