
ባሕርዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛው የናይል ቀን በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እየተከበረ ነው። በመርሐ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ግጭትን የሚፈቱና ትብብርን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል። ናይል የተስፋና የአንድነት ምልክት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የጋራ ኀላፊነትን መወጣት ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተፋሰሱ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ጎርፍ የሚቀንስ መኾኑን አንስተዋል። የናይል ወንዝ ተጋሪ ሀገራት የውኃ ሚኒስትሮች ቀጣናው ወደ ተሻለ ትብብር እንዲሻገር ጥሪ አቅርበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) የናይል ቤዝን ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን እና ትብብርን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ይህን እየተገበረች መኾኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ዓባይን የትብብር ማዕከል አድርጋ መሥራቷን እንደምትቀጥልም አመላክተዋል። ኢቢሲ እንደዘገበው
በአዲስ አበባ እየተከበረ ያለው የናይል ቀን ነገ በሕዳሴው ግድብ በሚደረግ ጉብኝት ይጠናቀቃል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!