ጎብኝዎች የሰው ዘር መገኛ እና የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የኾነችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም ጥሪ አቀረቡ።

28

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን እምቅ ታሪካዊ፣ ባሕላዊና ተፈጥሯዊ እሴቶችን የሚያስተዋውቅ መድረክ በዋሽንግተን ዲሲ ተካሂዷል።

የዝግጅቱ ዓላማ ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስክ ያላትን መስህብ ለአሜሪካውያን ለማስተዋወቅ እና ለጉብኝት እንዲጓዙ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ተብሏል።

በዝግጅቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም ኢትየጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት፣ ቡናን ለዓለም ያበረከተች እና በዩኔስኮ የተመዘገቡ አያሌ ቅርሶች ያሏት መኾኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ እጅግ ማራኪ እና ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻ ያላት መኾኗንም ገልጸዋል። በቱሪዝም ያላትን ዕምቅ ሀብት ሁሉም እንዲጎበኝ እና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የዝግጅቱ ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ በርካታ ባሕሎች፣ ልዩ ጣዕም ያላቸው የባሕል ምግቦች እና የሰው ዘር መገኛ እንደኾነች ለመረዳት መድረኩ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። መርሐ ግብሩ ሀገሪቱን የመጎብኝት ፍላጎት እንዳሳደረባቸውም ገልጸዋል።

በመድረኩ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕላዊ ዘፈኖች፣ ውዝዋዜዎች፣ የባሕል ምግቦች፣ አልባሳትና ጌጣጌጦችን የሚያስተዋውቅ ዝግጅት ለታዳሚዎች መቅረቡን ኢቢሲ ዘግቧል።

በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ አሜሪካውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ዲፕሎማቶች እና አርቲስቶች በመርሐ ግብሩ መገኘታቸውም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአህጉሩን የቡና አቅም የሚያሳድጉ ምርምሮችና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች አሳልፈናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“ናይል የተስፋና የአንድነት ምልክት ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ