
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በታንዛኒያ ዳር ኤስ ሰላም ከተማ የተካሄደው 3ኛው የG25 የአፍሪካ የቡና ጉባኤ ተሳትፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኮፊ አረቢካን ጨምሮ ዓለም ላይ ተፈላጊ የሆነ ባለ ልዩ ጣዕምና ጠንካራ የቡና ምርት መገኛው በአህጉራችን አፍሪካ ነው ብለዋል።
በታንዛኒያ ዳር ኤስ ሰላም ከተማ የተካሄደው 3ኛው የG25 የአፍሪካ የቡና ጉባኤ የአህጉሩን የቡና አቅም የሚያሳድጉ ምርምሮችና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች አሳልፈናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የቡና አምራች ሀገር እንደመሆኗ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበር ውጤት እያመጣች ትገኛለች ብለዋል።
”የአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪን በማነቃቃት ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን መክፈት” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው ጉባዔ ዘርፉን ለማነቃቃትና ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አመላል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት አራተኛውን የG25 የአፍሪካ የቡና ጉባኤ በ2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ እንዲካሄድ ተወስኗል ነው ያሉት። ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ዕድልም በታላቅ ኃላፊነት ተቀብለናል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!