“በማኅበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ ሥራ ነው” የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ

46

ደሴ: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችን በሚመለከት “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ ሀሳብ በደሴ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፣ በኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሳዳት ነሻ፣ የአማራ ክልል ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከለውጡ ወዲህ በከተማዋ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን እና ሕዝቡም ሀሳቡን በነጻነት የመናገር መብቱ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል።

ሆኖም የሕዝቡን ሰላም የሚነሱ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ እና መንግሥት በውስጡ ያሉ መሪዎችን እንዲፈትሽ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እና የአካባቢው የመሠረተ ልማት እጥረት እንዲስተካከል ጠይቀዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ደሴ ከተማ የበርካታ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሀብቶች ባለቤት ብትኾንም ለዘመናት የልማት ሥራዎች ተነፍገዋት እንደቆየች እና ከለውጡ በኋላ ግን መንግሥት እና ብልጽግና ፓርቲ ለከተማዋ ልማት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት የከተማውን የዘመናት የልማት ጥያቄ የሚመልስ እንደኾነ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የመብራት እና የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታዎች በክልል ብሎም በፌዴራል መንግሥት እገዛ እየተሠሩ ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሳዳት ነሻ ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚያረጋግጡ እንዲሁም ልማትን እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጸዋል።

መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መኾኑን እና በሰላም ለሚገቡ ሁሉ በሩ ክፍት መኾኑን አረጋግጠዋል።

ችግሮችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት የመንግሥት ፍላጎት መኾኑን ጠቁመው ሰላምን የማይፈልጉ እና የሕዝብን ደኅንነት የሚያወኩ ኀይሎች ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ርምጃ እንደሚወስድ ነው የተናገሩት።
የተነሱ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ መኾናቸውን እና መንግሥት በየደረጃው ምላሽ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግሥት እየሠራ መኾኑን እና ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የሚፈልጉ እና በተፈናቃዮች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሠሩ ኀይሎች ሥራውን እያደናቀፉ መኾኑን ጠቁመዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ የደሴ ከተማ እና አካባቢው ሕዝብ በሰላም እና በፍቅር እንደሚኖር ገልጸው ይህን ሰላም ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለመመለስ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

“በማኅበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አስተማማኝ ሰላምን ከሁሉ በፊት ማስፈን ቀዳሚ ሥራ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ የተደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። መንግሥት ሰላምን በማረጋገጥ የሀገርን ዕድገት ለማስቀጠል እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ሰይድ አብዱ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የአህጉሩን የቡና አቅም የሚያሳድጉ ምርምሮችና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች አሳልፈናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ