“የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

38

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመተግበር እና ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት በርብርብ መስራት እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርእሰ መሥተዳድሩ ይህን ያሉት በሸገር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሕዝብ ኮንፈረንስ ላይ ነው።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎችም ዘርፎች ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ወደ ከፍታ የሚወስዱና የሕዝቡን መሻት የሚያረጋግጡ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት።

ፓርቲው በ2ኛ መደበኛ ጉባዔው የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲሁም ሀገሪቱ በዓለም ተገቢውን ስፍራ እንድትይዝ የሚያደርጉ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካትና የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በርብርብ ማፋጠን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ.ር) ፓርቲው ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ገዥ ትርክት እንዲፈጠር እየሠራ ነው ብለዋል።

ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን በማዳበር ዘላቂ የሰላም ግንባታን ለማፋጠን አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፥ ለስኬቱ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ለሰላማዊ ውይይት ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ኃላፊ መሠረት አሰፋ ብልጽግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ጠቅሰው፣ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እንድታደርግ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በመደመር እሳቤ የተመዘገቡ ድሎችን በማስቀጠል የሀገር ግንባታ ግባችንን እናሳካለን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብን የሚያማርርን መሪ አይታገስም” ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር)
Next article“በማኅበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ ሥራ ነው” የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ