
የአገው ምሁራን ማኅበር 50 ሺህ 200 ብር ወጪ በማድረግ በባሕር ዳር ከተማ ለሚኖሩ አቅመ ደካሞች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ማኅበሩ 25 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብርሃይል ዛሬ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም አስረክቧል፡፡ ይህም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በሚደረገው እርዳታ ለአንድ ሰው በወር 15 ኪሎግራም ዱቄት ያስፈልጋል በሚለው ስሌት መሠረት በ30 ቀናት ውስጥ 166 ሰዎችን መመገብ ያስችላል፡፡
በርክክቡ ላይ ማኅበሩን ወክለው የተገኙት መላኩ መንግስቱ (ዶክተር ) ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በ“ቴሌግራም” ማኅበራዊ ገጽ በመፃፃፍና ገንዘብ በማሰባሰብ 400 ሺህ ብር የሚሆን ገንዘብ ወጪ በማድረግ የንጽህና መጠበቂያና የህክምና ቁሳቁሶችን ለአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንደለገሱ አውስተዋል፡፡ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ማኅበሩ ገቢ በማሰባሰብ በክልሉ ለሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር መላኩ አስታውቀዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወረርሽኙ በሀገሪቱ ከተከሰተ ጀምሮ በጥሬ ገንዘብና በአይነት 13 ሚሊዮን ብር የሚሆን ድጋፍ እንደሰበሰበ ምክትል ከንቲባ አማረ አለሙ ገልጸዋል፡፡ በአገው ምሁራን ማኅበርና በሌሎች የተለገሱትን ድጋፎች ሥራ በመቋረጡ ምክንያት የእለት ጉርሳቸውን መሸፈን ለሚቸገሩ ዜጎችና በኃይማኖት ተቋማት አካባቢ ለተጠለሉ ምንም ሥራ ለሌላቸው እንደሚውል ምክትል ከንቲባው አሳውቀዋል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት 48 ሺህ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የእለት ጉርሳቸውን ያጣሉ ተብለው እንደተለዩ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ