
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) ጠንካራ መሪ፣ ጠንካራ መንግሥት እና ጠንካራ ሕዝብ ካለ ሀገር ትሻገራለች ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የመሪ ግንባታ ላይ ጽኑ ውሳኔ ማሳለፉንም አስታውቀዋል። ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብን የሚያማርርን መሪ አይታገስም ነው ያሉት።
ጠንካራ መሪ ለመፍጠር እና ሕዝብን የሚያማርሩትን ደግሞ ለማየት በጋራ ኾኖ መታገል ይገባል ብለዋል። በርካታ መሪዎች ላይ ርምጃ መውሰዱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ እንሠራለንም ነው ያሉት። ፓርቲው የሀገርን አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያን እንገነባለን ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሀገር ግንባታ እና የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ነው ያሉት ኀላፊው ጥያቄዎቹ የሚፈቱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር፣ በሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደኾነ አስረድተዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ሁሉም ኢትዮጵያውያን የእኔ እንዲሏቸው እና አብረውም እንዲመልሷቸው ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የሚበጀን አንድነት፣ አብሮነት እና ፍቅር መኾኑን መግባባት አለብን ብለዋል። ሚዲያ ሀገር ያፈርሳል፣ ሀገርም ይሠራል ያሉት ኀላፊው ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም እና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስረድተዋል። በሀሰተኛ ሚዲያ ንግግር መደሰትም መከፋትም አይገባም፣ ትክክለኛውን መከታተል ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!