15 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የመንግሥት ሃብት ከብክነት ማዳኑን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

27

ጎንደር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ጎንደር ክላስተር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የመደበኛ እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ አካሂዷል።

ውይይቱ በጎንደር ክላስተር በሚገኙ የፍትሕ ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ የክልሉን የፍትሕ ተግባራት ገምግሟል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የፍትሕ ተቋማት ከፍተኛ ሚና መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሸም የማኅበረሰቡን የፍትሕ ጥያቄ ለማረጋገጥ፤ ቀልጣፋ ፍትሃዊ እና ቅቡል የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማዘጋጀት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ሥድስት ወራት የተተገበሩ የመደበኛ እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸምን በመገምገም ለቀጣይ የክልሉን የፍትሕ አገልግሎት በማዘመን ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ ተግባርን ለመከወን የምንግባባበት የውይይት መርኀ ግብር ነው ብለዋል።

ታማኝነት ያለው የፍትሕ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ለመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን በቴክኖሎጅ የማዘመን እና የተለያዩ የትራንስፎርሜሽን አዋጆችን የማጽደቅ ተግባር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

እንደ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ 47 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ማስመለስ መቻሉን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው ከወንጀል የተመዘበረ 337 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ሃብት ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

“15 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የመንግሥት ሃብት ከብክነት መታደግ መቻሉንም አንስተዋል።

ከ20 በላይ አቃቢ ሕጎችን በስነ ምግባር ምክንያት ተጠያቂ ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል።

የሰላም እጦት መኖር በፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና አሳድሮ እንደነበር ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡ በፍትሕ ተቋማት ብቻ ሳይኾን አገልግሎት በሚሰጡ ባለሙያዎች እምነት ያለው እንዲኾን በትዕግስት እና በሃቀኝነት ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ማኅበረሰቡ ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሰላም እጦት ዋጋ ከፍለናል፣ ከዚህ በኋላ ዋጋ መክፈል የለብንም” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next article“ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብን የሚያማርርን መሪ አይታገስም” ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር)