
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ኮንፈረንስ በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።
የሕዝባዊ ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የአማራ ክልል ሕዝብ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በፈተና እና በግጭት ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
ሕዝቡ ዋጋ ሲከፍል መቆየቱን የተናገሩት ተሳታፉዎቹ ጠላቶቻችን በሰጡን አጀንዳ ልማት እንዳናለማ፣ አንድነት እንዳይጠናከር፣ የሕዝብ ጥያቄ በሰላም እንዳይፈታ ኾኗል ነው ያሉት።
በተሠራው ሀሰተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ የልማት ሥራዎችን እንዳናደንቅ፣ ክፍተቱን ደግሞ በተገቢው መንገድ እንዳናመላክት አድርጎ ቆይቷል ብለዋል።
አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መሥራት እና የሰላም ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአንደኛው ክልል ያለው መሪ ወደ ሌላኛው ክልል ሄዶ ሕዝብን ማወያየት አንድነትን የሚያጠናክር እና የሕዝብን ዕውነተኛ ስሜት ለመረዳት የሚያስችል ነው ብለዋል።
እስካሁን የነበረው ልምድ በራስ ክልል እና አካባቢ ብቻ ተውሰኖ መወያየት ብቻ እንደነበርም አንስተዋል።
በከተሞች እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን መደገፍ ራስን መደገፍ መኾኑንም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የልማት ሥራዎች ሰላም ቢኾን ኖሮ ምን ያክል ልማት ሊሠራ እንደሚችል ቁጭት የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
የሰላም እና የጸጥታ ሥራውን በጥብቅ ቁጥጥር መምራት እና አንድነትን ማጽናት ይገባል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ሥራዎችን መታገል እና ሕዝብን ከምሬት መታደግ ይጠበቃል ብለዋል።
ገበያን መምራት እና መቆጣጠር ከመንግሥት እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራን ማጠናከር እና ብልሹ አሠራርን ማስተካከል ይገባልም ነው ያሉት።
ብቁ፣ ሕዝብ እና ሀገርን የሚያገለግሉ መሪዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለጥፋተኞች ተገቢውን ቅጣት መስጠት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚያሰቃዩ አካላትን ማስተካከል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የግብርና ግብዓቶች ሥርጭት ጤናማ እና ውጤታማ እንዲኾን መንግሥት እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱን ማስተካከል እና እውነተኛ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።
ሕዝብን የሚያማርሩ ችግሮችን መፍታት ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
መንግሥት እና ፓርቲው የሚገቡትን ቃል ሳያጓድሉ እንዲፈጽሙም ጠይቀዋል።
ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ሕዝብን እያናከሱት ያሉ የፖለቲካ ነጋዴዎችን ማስተካከል እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
መንግሥት ከሁሉም አስቀድሞ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ጉዳይ ተጠቃሚ ለመኾን ሰላምን ማረጋገጥ ቅደሚያ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!